About

ስለ ሀገር ቤት

ሀገር ቤት የእናት ቤት ነው፡፡ የመጨረሻ መጠግያ ዞሮ መግቢያ ቤት ነው ሀገር ቤት፡፡ በተለይ ደግሞ ሰው ከኖረበት ካደገበት ቀዬ ርቆ ሲኖር የሀገር ቤት ጥቅሙና ምንነቱ ውልል ብሎ ይገለፅለታል፡፡ ዛሬ ዛሬ ሰዎች ቢሰደዱም በዘመናዊነት ምክንያት ቴክኖሎጂውም እንደ ቀድሞ ባለመሆኑ በሀገር ቤት ያለው ነገር ሁሉ በሚኖሩበትም ቦታ ለማግኘት እንብዛም አይቸገሩም፡፡ አልያም ካደጉበት ከኖሩበት ከተወለዱበት ቦታ ከሞላ ጎደል ወደሚፈልጉበት ሀገር ያስመጣሉ፡፡ ሰዎች በሰው ሀገር ነገሩ ሰምሮ ታሪኩ አምሮ ቢያዩት ‹‹ ውይ ይኼማ ቁርጥ እንደ ሀገር ቤት አይደል እንዴ ›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እነሆ ታድያ አካላችን በሰው ሀገር ቢሆንም ሀገራችን በልባችን ነውና ሀገር ቤት ሀላፊነቱ የተወሰነ የመዝናኛ ድርጅት በሀገረ አሜሪካ ተቋቁሟል፡፡ የምናዘጋጀው ፕሮግራም ልክ እንደ ሀገር ቤት ሳይሆን ራሱ ሀገር ቤት ነው፡፡ በሀገር ቤት ሁሉ ሙሉ ነው፡፡ ማዕድ ቢጎል እንኳን ያለው ከሌለው ተካፍሎ መጥገቡ የሀገር ቤት ወጉ ነውና እነሆ አኛም ቤት ማዕዳችን ሙሉ ነው፡፡ ቢጎል እንኳን ያለንን ተካፍለን እንመገባለን እና ሀገር ቤት ብለነዋል፡፡

ሀገር ቤት ሀላፊነቱ የተወሰነ የመዝናኛ ድርጅት የሚሰራቸውን ስራዎች በሙሉ በእግር ሚዲያ ዩቱብ ቻናል የሚለቅ ሲሆን በቋሚነት በሀገረ አሜሪካ የሚያዘጋጀው ‹‹ ስደተኛው የስነ-ፅሁፍ ምሽት ›› የተሰኘ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት አለው፡፡


‹‹ ስደተኛው የስነ-ፅሁፍ ምሽት ››

‹‹ ስደተኛው የስነ-ፅሁፍ ምሽት ›› የተባለበት ምክንያት ሰዎች በተለያየ ምክንያት ተሰደው ከቀዬአቸው ከሀገራቸው ወደ ተለያየ ሀገር ይሄዳሉ፡፡ ሰዎች ሲሰደዱ አብሮ ሀሳባቸውም ራዕያቸውም ለጊዜውም ቢሆን ለዘለቄታው መሰደዱ አይቀሬ ነው፡፡ ሰዎች በስደት ሀገር ለስደተኛ አካላቸው ከሞላ ጎደል የሚያስፈልገውን ያሟሉለታል፡፡ ስደተኛ ሀሳባቸው ግን ሲደመጥ አይስተዋልም፡፡ ምንአልባት እነዚህ በየስደተኛው አዕምሮ ውስጥ የተቀበሩ ስደተኛ ሀሳቦች ቢደመጡ ዝቅ ሲል የግለሰብን ከፍ ሲል የማህበረሰብን ህይወት እና አስተሳሰብ መቅረፅና መቀየር የሚችሉ መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ እናም እነሆ የስደተኛውን ሀሳብ ልናደምጥ፣ ወግ ባህላችንን በስነ-ፅሁፍና በተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶች በማጋራት፣ በጋራ ራሳችን ለራሳችን ህመም እንደሆንን ሁሉ በጋራ መልሰን እኛው ለእኛው መድሀኒት ሆነን የምናክምበት ምሽት ሲሆን በዋናነት እንደማህበረሰብ የጋራ ስብራቶቻችንን በተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች የምናክምበት፣ ህብረታችንን፣አንድነታችንን የምናፀናበት ምሽት እንዲሆን በማሰብ ‹‹ ስደተኛው የስነ-ፅሁፍ ምሽት ›› እነሆ ብቅ ብሏል፡፡